Friday, February 12, 2010

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 1

ምዕራፍ 1።

1፤ በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የኢያሬምኤል ልጅ የኢሊዮ ልጅ የቶሑ ልጅ የናሲብ ልጅ ነበረ።

2፤ ሁለትም ሚስቶች ነበሩት፤ የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ፤ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፥ ለሐና ግን ልጅ አልነበራትም።

3፤ ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ።

4፤ ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው።

5፤ ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት። እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበር።

6፤ እግዚአብሔርም ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር።

7፤ በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፤ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር።

8፤ ባልዋም ሕልቃና። ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትቀምሺም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከአሥር ልጆች አልሻልልሽምን? አላት።

9፤ በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሣች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር።

10፤ እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች።

11፤ እርስዋም። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች።

12፤ ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።

13፤ ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፤ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት።

14፤ ዔሊም። ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት።

15፤ ሐናም። ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤

16፤ ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት።

17፤ ዔሊም። በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት።

18፤ እርስዋም። ባሪያህ በዓይንህ ፊት ሞገስ ላግኝ አለች። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች በላችም፥ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም።

19፤ ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤

20፤ የመፅነስዋም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርስዋም። ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው።

21፤ ሰውዮውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ።

22፤ ሐና ግን አልወጣችም፥ ባልዋንም። ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘላለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ አለችው።

23፤ ባልዋም ሕልቃና። በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ በቤትዋ ተቀመጠች።

24፤ ጡትም በተወ ጊዜ ከእርስዋ ጋር እርሱንና አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፤ ሕፃኑም ገና ታናሽ ነበረ።

25፤ ወይፈኑንም አረዱ፥ ሕፃኑንም ወደ ዔሊ አመጡት።

26፤ እርስዋም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በአንተ ዘንድ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ።

27፤ ሰለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤

28፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 1

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2

ምዕራፍ 2።

1፤ ሐናም ስትጸልይ እንዲህ አለች። ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛል።

2፤ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም።

3፤ አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ።

4፤ የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል።

5፤ ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች።

6፤ እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል።

7፤ እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል።

8፤ ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ።

9፤ እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል ኃጥኣን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይቀመጣሉ፤ ሰው በኃይሉ አይበረታምና።

10፤ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።

11፤ ሕልቃናም ወደ ቤቱ ወደ አርማቴም ሄደ፤ ብላቴናውም በካሁኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።

12፤ የዔሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር።

13፤ የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፤ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ ሎሌ ይመጣ ነበር፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፤

14፤ ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድድው ነበር፤ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ እንዲህ ያደርጉ ነበር።

15፤ ደግሞም ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ ሎሌ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው። ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ ይለው ነበር።

16፤ ሰውዮውም። አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት ኋላም ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ ቢለው፥ እርሱ። አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፤ እንቢም ብትል በግድ እወስደዋለሁ ይለው ነበር።

17፤ ሰዎቹም የእግዚአብሔርን ቍርባን ይንቁ ነበርና የጎበዛዝቱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች።

18፤ ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር።

19፤ እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፥ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ታመጣለት ነበር።

20፤ ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን። ለእግዚአብሔር ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ ብሎ ባረካቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ሄዱ።

21፤ እግዚአብሔርም ሐናን አሰበ፥ ፀነሰችም፥ ሦስት ወንዶችና ሁለትም ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

22፤ ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ።

23፤ እርሱም አላቸው። ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ?

24፤ ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም።

25፤ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው? እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም።

26፤ ብላቴናውም ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።

27፤ የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ አለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በግብጽ በፈርዖን ቤት ባሪያ ሳለ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤

28፤ ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፉድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።

29፤ በማደሪያዬ ያቀርቡት ዘንድ ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቍርባኔን ስለ ምን ረገጣችሁ? እንድትወፍሩም የሕዝቤን የእስራኤልን ቍርባን ሁሉ መጀመሪያ በመብላታችሁ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ?

30፤ ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእውነት ቤትህ የአባትህም ቤት ለዘላለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም።

31፤ እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ ክንድህን የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል።

32፤ በእስራኤል በረከት ሁሉ፥ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ በቤትህም ለዘላለም ሽማግሌ አይገኝም።

33፤ ከመሠዊያዬ ያልተቈረጠ ልጅህ ቢገኝ ዓይንህን ያፈዝዘዋል፥ ነፍስህንም ያሳዝናል ከቤትህም የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ በጐልማስነት ይሞታሉ።

34፤ ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ።

35፤ የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፥ በልቤም በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፤ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል።

36፤ ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፥ በፊቱም ሰግዶ፥ ቍራሽ እንጀራ እበላ ዘንድ ከካህናት ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ አንድ ብር አንድ እንጀራም ይለምናል።

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3

ምዕራፍ 3።

1፤ ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር።

2፤ በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር።

3፤ ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥

4፤ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።

5፤ ወደ ዔሊም ሮጠ። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ።

6፤ እግዚአብሔርም ደግሞ። ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ።

7፤ ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።

8፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ።

9፤ ዔሊም ሳሙኤልን። ሄደህ ተኛ ቢጠራህም። አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ።

10፤ እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም። ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም። ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው።

11፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ።

12፤ በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ።

13፤ ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ።

14፤ ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።

15፤ ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ።

16፤ ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ። ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።

17፤ እርሱም። እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው።

18፤ ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም። እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።

19፤ ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር።

20፤ እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ።

21፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 4

ምዕራፍ 4።

1፤ እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያን በአፌቅ ሰፈሩ።

2፤ ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፤ ሰልፉም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ።

3፤ ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች። ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄዱ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ።

4፤ ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።

5፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች።

6፤ ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ። በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ።

7፤ ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው። እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ። ወዮልን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም።

8፤ ወዮልን፤ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው።

9፤ እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ።

10፤ ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ።

11፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።

12፤ በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ።

13፤ በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፤ ሰውዮውም ወደ ከተማይቱ ገብቶ ባወራ ጊዜ ከተማይቱ ሁሉ ተጭዋጭዋኸች።

14፤ ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ ጫጫታ ምንድር ነው? አለ። ሰውዮውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው።

15፤ ዔሊም የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ ዓይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር።

16፤ ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው።

17፤ ወሬኛውም መልሶ። እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ።

18፤ ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፤ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት ፈራጅ ነበረ።

19፤ ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች።

20፤ ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም።

21፤ እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው።

22፤ እርስዋም። የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች።

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 5

ምዕራፍ 5።

1፤ ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱ፤ ከአቤንኤዘርም ወደ አዛጦን ይዘውት መጡ።

2፤ ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት።

3፤ በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት።

4፤ በነጋውም ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር፤ የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር።

5፤ ስለዚህም የዳጎን ካህናት ወደ ዳጎንም ቤት የሚገቡት ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም።

6፤ የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፥ አጠፋቸውም፥ አዛጦንንና ድንበራቸውንም በእባጭ መታቸው።

7፤ የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ። እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ።

8፤ ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ወደ እነርሱ ሰበሰቡና። በእስራኤል አምላክ ታቦት ምን እናድርግ? አሉ፤ እነርሱም። የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይዙር ብለው መለሱ። የእስራኤልንም አምላክ ታቦት ወደዚያ ተሸከሙት።

9፤ ከተሸከሙትም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በታላቅ ድንጋጤ በከተማይቱ ላይ ሆነች፤ ከታናሹም እስከ ታላቁ ድረስ የከተማይቱን ሰዎች መታ፥ እባጭም መጣባቸው።

10፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት ወደ አስቀሎና ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና በመጣ ጊዜ አስቀሎናውያን። እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመጡብን ብለው ጮኹ።

11፤ በከተማይቱ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበርና፥ የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ እጅግ ከብዳ ነበረችና ልከው የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥ እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመለስ አሉ።

12፤ ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 6

ምዕራፍ 6።

1፤ የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን አገር ሰባት ወር ተቀመጠ።

2፤ ፍልስጥኤማውያንም ካህናትንና ምዋርተኞችን ጠርተው። በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ምን እናድርግ? ወደ ስፍራውስ በምን እንስደደው? አስታውቁን አሉ።

3፤ እነርሱም። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰድዱ የበደል መሥዋዕት መልሱለት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፥ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አሉ።

4፤ እነርሱም። ስለ በደል መሥዋዕት የምንመልስለት ምንድር ነው? አሉ። እነርሱም እንዲህ አሉ። እናንተንና አለቆቻችሁን ያገኘች መቅሠፍት አንዲት ናትና እንደ ፍልስጥኤማውያን አለቆች ቍጥር አምስት የወርቅ እባጮች አምስትም የወርቅ አይጦች አቅርቡ።

5፤ የእባጫችሁንም ምሳሌ፥ ምድራችሁንም የሚያጠፋአትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ፤ እጁን ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ ከምድራችሁም ምናልባት ያቀልል ይሆናል።

6፤ ግብጻውያንና ፈርዖንም ልባቸውን እንዳጸኑ ልባችሁን ለምን ታጸናላችሁ? እግዚአብሔር ኃይሉን ካደረገባቸው በኋላ ያወጡአቸው አይደሉምን?

7፤ እነርሱም አልሄዱምን? አሁንም ወስዳችሁ አንዲት ሰረገላ ሥሩ፤ የሚያጠቡም፥ ቀንበር ያልተጫነባቸውን ሁለት ላሞች በሰረገላ ጥመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም ለይታችሁ ወደ ቤት መልሱአቸው።

8፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩት፤ ስለ በደልም መሥዋዕት ያቀረባችሁትን የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቱ አጠገብ አኑሩት፤ ይሄድም ዘንድ ስደዱት።

9፤ ተመልከቱም በድንበሩም መንገድ ወደ ቤትሳሚስ ቢወጣ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ያደረገብን እግዚአብሔር ነው፤ አለዚያም እንዲያው መጥቶብናል እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን።

10፤ ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ፤ የሚያጠቡትን ሁለቱን ላሞች ወሰዱ፥ በሰረገላም ጠመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም በቤት ዘጉባቸው፤

11፤ የእግዚአብሔርም ታቦት፥ የወርቁ አይጦችና የእባጮቻቸው ምሳሌ ያሉበትንም ሣጥን በሰረገላው ላይ ጫኑ።

12፤ ላሞችም ወደ ቤትሳሚስ ወደሚወስደው መንገድ አቅንተው እምቧ እያሉ በጎዳናው ላይ ሄዱ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላሉም፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች እስከ ቤትሳሚስ ዳርቻ ድረስ በኋላ በኋላቸው ይሄዱ ነበር።

13፤ የቤትሳሚስ ሰዎችም በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፤ ዓይናቸውንም ከፍ አድርገው ታቦቱን አዩ፥ በማየታቸውም ደስ አላቸው።

14፤ ሰረገላውም ወደ ቤትሳሚሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ መጣ፥ ታላቅም ድንጋይ በነበረበት በዚያ ቆመ፤ የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።

15፤ ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ፥ በታላቁም ድንጋይ ላይ አኖሩት፤ በዚያም ቀን የቤትሳሚስ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ መሥዋዕትንም ሠዉ።

16፤ ፍልስጥኤማውያንም አምስቱ አለቆች ባዩት ጊዜ በዚያው ቀን ወደ አስቀሎና ተመለሱ።

17፤ ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡአቸው የወርቅ እባጮች እነዚህ ናቸው፤ አንዲቱ ለአዛጦን፥ አንዲቱም ለጋዛ፥ አንዲቱም ለአስቀሎና፥ አንዲቱ ለጌት፥

18፤ አንዲቱ ለአቃሮን የወርቁም አይጦች ቍጥር ለአምስቱ የፍልስጥኤማውያን አለቆች እንደ ነበሩት ከተሞች ሁሉ ቍጥር እንዲሁ ነበረ፤ እነርሱም እስከ ታላቁ ድንጋይ የሚደርሱ ከተሞችና መንደሮች ናቸው። በዚህም ድንጋይ ላይ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡ፥ ድንጋዩም እስከ ዛሬ ድረስ በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ እርሻ አለ።

19፤ ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ።

20፤ የቤትሳሚስም ሰዎች። በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? አሉ።

21፤ በቂርያትይዓሪምም ወደ ተቀመጡት ሰዎች መልክተኞች ልከው። ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰዋል፤ ወርዳችሁም ወደ እናንተ አውጡት አሉ።